የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣንና የራሽያው አቻ ተቋም የፌደራል አካባቢ ኢንዱስትሪና ኑክሌር ሱፐርቪዥን ሰርቪስ (Rostechnadzor) በጨረራና ኑክሌር መሰረተ-ልማት ቁጥጥር ዙሪያ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈረመ፡፡ የጋራ መግባቢያ ስምምነቱ የተፈረመው ጥር 29 / 2016 በአዲስ አበባ ከተማ አዜማን ሆቴል ሲሆን ስምምነቱን የፈረሙት ደግሞ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው እና የራሽያው አቻቸው ሚስተር አሌክሳንድሮ ናቸው፡፡ በፊርማ ስነስርዓቱ ወቅት እንደተገለጸው ስምምነቱ ለሁለቱ ተቋማት በአቅም ግንባታ ዘርፍ፣ ልምድና ዕውቀት ልውውጥ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ስነ-ስርዓቱን በንግግር የከፈቱት ዶ/ር ፎዚያ የኢኒቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚ/ቴር ሚኒስትር ዴታ እና በራሽያ በኩል ደግሞ የRostechnadzor ሃላፊ ሚስተር አሌክሳንድሮ ናቸው፡፡ በጋራ መግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስርዓቱ ላይ ሁለቱ ሃላፊዎች ባቀረቡት ንግግር የጋራ መግባቢያ ስምምነቱ ለፈራሚዎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ተጠቁሟል

አህጉራዊ ወርክሾፕ በመካሄድ ላይ ነው

በአለምአቀፉ አቶሚክ ኢነርጅ ኤጀንሲ (International Atomic Energy Agency) እና በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን (Ethiopian Technology Authority) ትብብር ቴክኒካዊ አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት የአገልግሎት ፈቃድ በመስጠት ሂደት ሊተገበሩ በሚገባቸው የአለምዓቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የጥንቃቄ ስታንዳርዶች አስገዳጅ ሁኔታዎችና መመሪያዎች (Workshop on the requirement and guidance of the IAEA Safety Standards for the authorization by the regulatory bodies of technical service providers) ላይ ያተኮረ አህጉራዊ ወርክሶፕ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ ወርክሾፑ ከመስከረም 7-10/2016 የሚቆይ ሲሆን የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ከተለያዩ የአለምዓቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ አባል ሀገራት የተወጣጡ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ወርክሾፑ በመካሄድ ላይ የሚገኘው በመዲናችን አዲስ አበባ ሲሆን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው ወርክሾፑ በሚካሄድበት ካሌብ ሆቴል በመገኘት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በይፋ ተጀምሯል፡፡ የወርክሾፑ ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታና ተሳትፎ ብዙ የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በራዲዮሎጂካልና ኑክሌር ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን በራዲዮሎጂካልና ኑክሌር ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ለተቀዳሚ ምላሽ ሰጭ ባለድርሻ አካላትና ለሚመለከታቸው የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ከየካቲት 29/06-04/07/2015 ዓ.ም ድረስ በአዳማ ከተማ ካኔት ሆቴል ስልጠና ሰጠ::

የኡጋንዳ ሪፑብሊክ ፓርላማ አባላት ኦፊሴላዊ የስራ ጉብኝት አደረጉ

የኡጋንዳ ሪፑብሊክ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የካቲት 16/2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን መ/ቤት የስራ ጉብኝት አደረጉ፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ስለ መስሪያ ቤቱ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ዓላማዎች፣ ተልዕኮዎችና አሁናዊ ሁኔታ ዝርዝር ገለጻ የቀረበላቸው ሲሆን ገለጻውን ተከትሎም በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት በፓርላማ አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ለቀረቡ ጥያቄዎችም እንደየአግባቡ በባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች መልስና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በነበራቸው የስራ ጉብኝት ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን እንዳገኙ የገለጹ ሲሆን እንደዚህ ዓይነት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ያላቸው ስለመሆኑም አንስተዋል

የባለስልጣኑ ማኔጅመንት አባላት የተተከሉ ችግኞችን ጎበኙ

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ማኔጅመንት አባላት ቀደም ሲል በአረንጓዴ አሻራ ማስቀመጥ ፕሮግራም በሰሜን ሸዋ ልዩ ስሙ መንዲዳ በሚባለው ቦታ በመገኘት በሰራተኞች የተተከሉ ችግኞች የሚገኙበትን ሁኔታ በአካል በመገኘት የጎበኙ ሲሆን ችግኞች በቀጣይ ለሚያስፈልጋቸው የውሃ አቅርቦት የሚያግዝ የውሃ ፓምፕ ሞተርና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለወረዳ አስተዳደሩ በድጋፍነት አበርክተዋል፡፡ የማኔጅመንት አባላቱ ጉብኝቱን ያካሄዱት ጥር 25/ 2015 ዓ.ም ሲሆን ወደፊት በሚደረጉ የድጋፍና ትብብር ስራዎች ላይም ከወረዳ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ውይይትና የጋራ የመስክ ምልከታ መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡